Fana: At a Speed of Life!

ከተማዋን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩ ትልቅ እመርታ ነው – የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተማዋን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩ ትልቅ እመርታ ነው አለ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ማሩ ጃኔ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ምክር ቤቱ ለጋራ ምክር ቤት አባላት ዕጩዎች፣ ለፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በምርጫው ገንቢ ሚና መጫወት የሚያስችላቸውን ስልጠና በቀጣይ እንደሚያመቻችም አመልክተዋል።

አሁን ላይ ከተማዋን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩ ትልቅ እመርታ ነው ብሎ ምክር ቤቱ ያምናል ያሉት ሰብሳቢው÷ ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ በነፃነት ለማቅረብ አስችሏል ብለዋል፡፡

ፓርቲዎች ለዘንድሮ ምርጫ እጩ በማስመዝገብና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላደረጉት ንቁ ተሳትፎ በምክር ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዘሪሁን ኮርሜ በበኩላቸው÷ ምርጫው በአዲስ አበባ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ምክር ቤቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ፓርቲዎች በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችና ክፍተቶችን በውይይትና ሀገርን ባስቀደመ መልኩ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ በማውጣት ይወክለኛል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.