Fana: At a Speed of Life!

መደመር – የለውጡ መንግሥት ፍኖተ ካርታ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጡ እውን መሆኑን ተከትሎ በ’መደመር’ መርህ የነበሩ ወረቶችን እና አዳዲስ ዕሳቤዎችን አቀናጅቶ የላቀ ዐቅም መፍጠር እንደሚቻል በማሳየት ባለፉት ስምንት ዓመታት መንግሥት በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፉት መደመር፣ የመደመር መንገድ፣ የመደመር ትውልድ እና የመደመር መንግሥት መጻሕፍት የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ እሴቶችን በማቀናጀት ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ የሚሆኑ ሐሳቦችን በመዳሰስ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

መጻሕፍቱም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን በመለየት የሚጠቁሙ በመሆናቸው ያሳለፍናቸውንና እያሳለፍናቸው ያሉ ችግሮችን ምንጭ ከነምክንያቱ የሚያስቀምጡ ናቸው።

አብዛኞቹ ችግሮች ከውጪ የተቀዱ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን እንደወረደ ለመተግበር ሲሞከር የሚከሰቱ መሆናቸውን በማመላከትም ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄው አካል በመሆን ለውጡ ሀገርን የሚያሻግር መሆን እንዳለበት አጽንኦት የሰጠ ነው።

ይህም መሬት የወረዱ ውጤቶችን በማስመዝገብ ውጤቶቹ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚጨበጡ ሆነው ተቀምጠዋል።

የመደመር ፍልስፍና ኢትዮጵያውያን ተደምረው አንድነቷ የተጠበቀ እና የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ያለው ሚናን አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን÷ ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንዲችሉ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው።

የመደመር እሳቤ ሰውኛ ጉዳዮችን በማጉላት የሰውንና የተፈጥሮን መደጋገፍ የሚሳይ እንዲሁም አብሮ መቆየትና መደጋገፍ ለጥንካሬያችን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ የሚያስገነዝብም ጭምር ነው።

አንዱ ለሌላው ወሳኝ በመሆኑ መደመር እና መደጋገፍን ለአንድነትና ለጥንካሬ ምንጭ በማድረግ የበለፀገች ሀገርን ለመገንባት መትጋት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባል።

መደመር የኢትዮጵያን የቀደመ የፖለቲካ የጽንፎች ክረት ለማርገብ አማራጭ በመሆን ለአዲስ የፖለቲካ ውይይት በር የከፈተና ተራማጅ በመሆን ከተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች በጎውን ወስዶ ከሀገራችን እውነታ ጋር ያጣጣመ እንደሆነም ይገለጻል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.