በአዲስ አበባ ከተማ ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍ ህዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።
የሰልፉ ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመጋቢት 24 ተምሳሌታዊ ጉዞ እና መሰረታዊ ርምጃ የተመዘገቡ ስኬቶችን እያደነቁ ነው።
በለውጡ መንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን በመደገፍ፣ በቀጣይም የተሻለ ስራ እንዲሰራ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የሚያረጋግጡ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።
በዚህም በመጋቢት 24 ፍሬ ወደ ተምሳሌታዊ ጉዞ፣ ጠንካራ መሰረት የተምሳሌትነት ጉዞ ስንቅ፣ መሰረት ባለው ርምጃ ወደ ተምሳሌትነት፣ መጋቢት 24 የተምሳሌታዊነታችን መሰረትና መፍለቂያ ነው፣ መጋቢት 24 ሀገር ከመፍረስ የዳነችበት የታሪክ ምዕራፍ የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም የመጋቢት 24 ፍሬዎች የተምሳሌትነት ጉዞ የትውልድ ብልፅግና ነው፣ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ለውጥ መነሻና ብልፅግና መሠረት ነው፣ መጋቢት 24 በመስዋዕትነት መጣ በመስዋዕትነት እንጠብቀዋለን፣ አስተሳሳሪ እና የወል ትርክታችን ለዘላቂ አንድነት እና አብሮነታችን የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።