መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል – ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ዘርፉን ማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ የ2018/19 የበልግና የመኸር ወቅት የሰብል ልማት የንቅናቄ መርሐ ግብርን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን በሰጡት መግለጫ፥ በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የመሬትና የውሃ ሃብት እንዲሁም ሌሎች ፀጋዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ የግብርና ዘርፉን በማዘመን ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፥ የተሻሻሉ ፖሊሲዎችና የተለያዩ የግብርና መርሐ ግብሮች ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ በቅንጅት ባደረጓቸው ጥረቶች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንና በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡
በተለይም የእርሻ ልማትና የመስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበባቸው የግብርና ዘርፎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም በሰብል ልማት ምርታማነትን የማሳደግ እንዲሁም የሚታረሱ የእርሻ መሬቶችን የመጨመር እንዲሁም የአፈር ጥበቃ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት