የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታ ተቋሞችን ችግር ወደ ዕድል እንዲቀየሩ አስችለዋል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታ ተቋሞችን ችግር ወደ ዕድል እንዲቀየሩ አስችለዋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
“የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት” በሚል መሪ ሀሳብ ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፍረንስ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የሰላም ጋሻ፣ የብሔራዊ ክብርና ጥቅማችን ዘብ ናቸው ብለዋል።
በቀጣናችን የሚስተዋሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ የአሸባሪ ቡድኖች ሴራ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ሀገራችንን ቢፈትኑም፤ በፀጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ጥንካሬና በልጆቿ መስዋዕትነት ለአፍሪካ ፋና ወጊ የሚሆን ተግባር በመፈፀም ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ ጸንታ ቆማለች ነው ያሉት።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ችግርን ወደ ዕድል እንዲቀየሩ ያስቻሉ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት የዘመኑት የጸጥታ ኃይሎቻችን ሌት ተቀን ትጋት እና በህዝባችን አጋርነት ሀገራዊ ሁለንተናዊ ውጤት ማስመዝገብ ያስቻለን ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውንም ገልጸዋል።
ይህን ስኬት ለማስመዝገብ በየደረጃው የሚገኙ የፌደራል የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም የክልል የፀጥታ ተቋማት ቅንጅትና የጋራ ጥረት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላም ለማስፈን የተኬደባቸው ርቀቶችና የተገኙት ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትና የሕዝቡ የተቀናጀ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲ የሚጸናበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንዲሆን የጸጥታ ተቋሞች ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ ያላቸውን የጸና እምነት ገልጸዋል።
ጉዟችን ተጀመረ እንጂ አልተቋጨምና ከትናንት ዕዳዎች ተላቀን፣ የዛሬ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ለነገው ትውልድ የምትመጥን ሀገር ለመገንባት በዓላማ ጽናት እንቀጥላለን ሲሉ አንስተዋል።
ለሀገር ህልውና መስዋዕትነት ለከፈሉና ሌት ተቀን ለሚተጉ የጸጥታና ደኅንነት አመራሮችና አባላቶቻችን እንዲሁም በሀገሩ ጉዳይ ለማይደራደረው ለጀግናው ሕዝባችን ያለኝን ጥልቅ አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ ነው ያሉት።