Fana: At a Speed of Life!

በሴፍቲኔት የሚደገፉ አርሶ አደሮች ወደ ስንዴ አምራችነት በመግባታቸው ከተረጂነት ተላቅቀዋል – የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሴፍቲኔት መርሐ ግብር ይደገፉ የነበሩ አርሶ አደሮች ወደ ስንዴ አምራችነት በመግባታቸው ከተረጂነት ተላቅቀዋል አሉ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ፡፡

በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ የሰብል ልማት ወቅታዊ ቁመና እና እንክብካቤ እንዲሁም ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ ማስጀመሪያና የመስክ ጉብኝት ተደርጓል።

አቶ ጌቱ ገመቹ በወቅቱ እንዳሉት፤ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ በሀገር ደረጃም ሆነ በክልሉ ትልቅ ለውጥ መጥቷል፡፡

በክልሉ ከዝናብ ተኮር ወደ መስኖ በተቀየሰው ፖሊሲ መሠረት 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በበጋ ስንዴ ልማት መሸፈኑን ገልጸው፤ 150 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በክረምት የእርሻ ወቅት ደግሞ ከ109 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ በዚህም የበጋ ስንዴ አጠቃላይ ምርት ከክረምቱ መብለጡን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በሴፍቲኔት መርሐ ግብር ይደገፉ የነበሩ አካባቢዎች አሁን የስንዴ አምራች እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ከተረጂነት ወጥተው ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የበጋ መስኖ ሥራን ለማጠናከር የከርሰ ምድር ውሃ የማውጣት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጋ ስንዴ የተመዘገበው ውጤት ሀገሪቱ በተለመችው ስትራቴጂ መሰረት የብልፅግና መዳረሻዋን የሚጠቁም ነው ብለዋል።

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.