Fana: At a Speed of Life!

ዘመናዊ የምርምር ማዕከሉ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እናያለን ብለን የማናስባቸውን በርካታ አቅሞች ይዟል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመናዊ የምርምር ማዕከሉ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እናያለን ብለን የማናስባቸውን በርካታ አቅሞች ይዟል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ የተገነባው ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ሰፊ ኢንቨስትመንት ተደርጎ የተሰራ ላቦራቶሪ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ላቦራቶሪው በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እናያለን ብለን የማናስባቸውን በርካታ አቅሞች ይዟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ከ2 ሚሊየን ያላነሱ ናሙናዎችን መያዝ የሚያስችል ላቦራቶሪ መገንባቱን ተናግረዋል።

ኮሮና ሲፈጠር ብዙ ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላክ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ለምርመራው የሚያስፈልጉ እውቀቶች በመሳሪያም በሰው ኃይልም በአዲሱ የምርምር ማዕከል እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የምርምር ሂደቱ ሳይንስና አካባቢያዊ አቅምን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም ሌሎች ፊልዶችን ለመርዳት በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በእውቀትና በቴክኖሎጂ የደረጀ ለብዙዎቹ ምርቶች ግብዓት የሚሆን ተቋም ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ዛሬ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ያየነው ላቦራቶሪ ብቃት፣ የሰው ኃይል መነሳሳትና የተገኘው ውጤት በቀጣይ ዓመታት ለማሳካትና በመድኃኒት ራስን የመቻል ፍላጎታችንን በተሟላ ደረጃ ለመከወን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.