Fana: At a Speed of Life!

ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን – ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን አሉ ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የከተማችንን እድሳት ለማፋጠን እና የዜጎቻችንን ክብር ለመመለስ የገባነውን ቃል አንዱ ማረጋገጫ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀን ከፍተናል ብለዋል።

በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶችን በፓርኩ መሃል በማቆም የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪ ትውልድ ስፖርተኞች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋልም ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና የሜዳ ቴኒስ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እያንዳንዱ የማዕከሉ ክፍሎች የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ መገንባቱንም አመልክተዋል።

‎የእውነተኛ ልማት ማዕከል ማህበረሰቡ ላይ መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህ ፕሮጀክት ከላቀ የስፖርት አገልግሎት ባለፈ፣ በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆችን እንዲሁም 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ ይዟል ብለዋል።

በአንዴ 300 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት መኪና ማቆሚያ ያለውና ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር የተሳሰረው ፓርኩ÷ ንፁህና ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የጀመርነውን ቁርጠኝነት ጉልህ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን ሲሉም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.