ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት መስራቷን ትቀጥላለች – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት በቁርጠኝነት መስራቷን ትቀጥላለች አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሰአድ ሙባረክ አል-ናይሚ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች፣ በኢንቨስትመንት መስፋፋት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ የልማት ስራዎች ዙሪያ በዝርዝር መምከራቸውን ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችንና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን በተመለከተ ማብራራታቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ እንደ የኮሪደር ልማት፣ የግብርና ምርታማነት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ያላቸውን ሚና አንስተናል ብለዋል።
የኳታር መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ አደም÷ ኢትዮጵያ ለሰፊ ኢንቨስትመንትና ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጫለሁ ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ብልፅግና ፓርቲ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጫለሁ ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ በማሳደግ፣ ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት በቁርጠኝነት መስራቷን ትቀጥላለች ሲሉም አስረድተዋል።
አምባሳደሩም በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየተመዘገበ ያለው ውጤት አመርቂ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በሀገሪቱ ውስጥ ተገማች፣ ግልጽና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፈጠሩን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በጎበኟቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችም የልማት ስራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆኑ መታዘባቸውን ገልጸዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የኳታሩ ሹራ ካውንስል (Shura Council) ከብልፅግና ፓርቲ እና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችልባቸው መንገዶች ላይ መምከራቸውን አመልክተዋል።