Fana: At a Speed of Life!

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ አሳድጓል – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ አሳድጓል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፡፡

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ18 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያ ሪፓርት ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋና ዋና ዘርፎች ውጤት ማሳየት መጀመሩን ገልጸው÷ የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ፣ የውጭ ንግድ እንዲያድግ እና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ዕድል መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 2023 እስከ 2024 ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 08 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቷን ጠቁመው÷ ከ2024 እስከ 2025 መጨረሻ ወደ 8 ነጥብ 33 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቷን አብራርተዋል፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፋይናንስ፣ በንግድ እና በሌሎች ዘርፎች የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን በማስቀረት ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በብዝኃ ዘርፍ የተዘረጋው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአስተማማኝ የዕድገት ፍጥነት ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ይህም ውጤታማ የዲጂታል የመረጃ አያያዝ እና የተቋማት ቅንጅት የታየበት ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት አንፃር የሚታይና የሚዳሰሰ ውጤትና ሥርዓት ለመገንባቷ ሪፖርቱ ማጣቀሻ እንደሚሆን የገለጹት ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው።

ይህንን በማጠናከር ረገድ ኢኮኖሚ የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ክትትል እየተደረገለት መሆኑን አረጋግጠዋል።

በክብረወሰን ኑሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.