Fana: At a Speed of Life!

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በወጪ ንግድ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ እመርታ አምጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የ2026 የፀደይ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በንግግራቸው ኢትዮጵያ አሁን ያለውን አስቸጋሪ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አቅርቦት በራሷ አቅምና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድንገተኛ ችግሮችን እንዴት እየተቋቋመች እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተመን አሰራርን በማጠናከር፣ የገንዘብ ፖሊሲን በማዘመን እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ የጀመረቻቸው ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ማሻሻያዎች የወጪ ንግድ እንዲያድግ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲሻሻልና የመንግሥት ገቢ እንዲጨምር በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በግል ዘርፍ የሚመራ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።

ሀገር በቀል ማሻሻያዎች ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ቢሆኑም፤ አሁንም እንደ አይ ኤም ኤፍ ካሉ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር የሚደረግ የተቀናጀ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገዥው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ እያጋጠሙ ያሉ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ረገድ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመጠበቅ፣ ማሻሻያዎችን ለማስቀጠል እንዲሁም ይበልጥ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.