ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደምትችል ለማሳየት ታቅዷል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አለም አቀፋዊ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደምትችል ለዓለም ለማሳየት ታቅዷል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኮፕ 32 ስትራቴጂክ ዕይታና እስካሁን ያለውን የቅደመ ዝግጅት ሥራ በተመለከተ ለኮፕ32 ብሔራዊ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸው በጉባዔው የውይይት አጀንዳዎች ላይ ድርድር በማድረግ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም፣ የሚታወስ እና የሚዘከር ውጤት ለማምጣት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በመስተንግዶ፣ በሎጂስቲክስና ኦፕሬሽን የተዋጣለትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደምትችል ለዓለም ለማሳየት ታቅዷል ነው ያሉት፡፡
በጉባዔው ከአየር ንብረት ለውጥ እና ታዳሽ ሃይል ጋር በተያያዘ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲያድግና የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ማድረግ በጉባዔው የተቀመጠ ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ማሳየት እንዲሁም በሁነቱ የሚሳተፉ የሀገራችን ባለሙያዎች፣ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አቅም ማጎልበትና ልምድ መቅሰም ከጉባዔው ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ