Fana: At a Speed of Life!

የኮፕ32 ጉባዔ ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለውን አረንጓዴ ኢነርጂ ለሌሎች የምናጋራበት ነው – ፍሬህይወት ታምሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮፕ32 ጉባዔ ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለውን አረንጓዴ ኢነርጂና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን ለሌሎች የምናጋራበት ነው አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ32) ብሔራዊ ኮሚቴ የተከናወኑ ሥራዎችን ገምግመዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚህ ወቅት÷ የዲጂታል፣ አይሲቲ እና ዩቲሊቲ ግብረ ኃይል ያከናወናቸው ጉዳዮችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ግብረ ኃይሉ የኮፕ 32 ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ቁልፍ የአስቻይ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰዋል።

በፈታኝ ሁኔታዎች የማይበገር ጠንካራ፣ አስተማማኝ፣ የተናበበ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ከመሰረተ ልማት እስከ ዲጂታል አገልግሎት የማቅረብ ተልዕኮ እንዳለውም አመልክተዋል።

ጉባዔው ሀገሪቱ እየተጠቀመች ያለውን አረንጓዴ ኢነርጂና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕድገትና ውጤት ለሌሎች የምናጋራበትና የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብርት ለውጥን ለመቋቋም እየሰራች ያለውን ስራዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚሰራበት መድረክ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የቴሌኮም አገልግሎት፣ የኃይል አቅርቦት፣ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት እና ኮፕ የሚመራበት ዲጂታል ሥርዓት እንደሚዘረጋ አንስተዋል።

ለጉባኤው አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሰረተ ልማቶችና ዲጂታል አገልግሎቶች በሙሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አቅምን የታጠቁ እንዲሆኑና ሁለንተናዊ የሳይበር ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የማስቻል ስራዎችን ግብረ ኃይሉ እንደሚያከናውንም ገልጸዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.