የአምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ አምባሳደሮች እና ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ቆንጂት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ1950ዎቹ ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል።
በኦቶዋ፣ ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬዬና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት÷ በአፍሪካ ሕብረትና በተባባሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ መልዕክተኛ በመሆንም ሰርተዋል።
ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይ ልዩ አማካሪ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
አምባሳደር ቆንጂት በ1932 ዓ.ም በሐረር ከተማ የተወዱ ሲሆን÷ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።
በጀማል አህመድ