Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ የልማት ግቦች ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ የልማት ግቦች ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤአተ ሜይንል-ራይዚንገር ጋር ተወያይተዋል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ እንዲሁም እንደ የታዳሽ ኃይል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል መሠረተ ልማት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን አብራርተዋል።

ቤአተ ሜይንል-ራይዚንገር በበኩላቸው÷ ኦስትሪያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግና የንግድ ለንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ገልጸዋል።

የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑካንን ጉብኝት ለማመቻቸት፣ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በክህሎት ልማት ተቋማዊ አጋርነትን ለማሳደግ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰው÷ ዛሬ በተካሄደው የኢውሮፓ ሕብረት-ኢትዮጵያ የንግድ ፎረም ላይ የኦስትሪያ ኩባንያዎች ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ሚኒስትሮቹ በባለብዙ ወገን ትብብር ረገድ ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ የልማት ግቦች ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን÷ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ትምህርት፣ ባሕል እና በባለብዙ ወገን ዘርፎች ሰፊ የትብብር ዕድሎች መኖራቸውን መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.