Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው አሉ።

ፕሬዚዳንት ታዬ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ ጋር በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ዘመናት የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ሕብረቱ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኃይል ልማት በመደገፍ እያበረከተ ለሚገኘው አስተዋጽኦም ምስጋና ያቀረቡት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ በቀጣይም የኢትዮጵያን የልማት ዕድሎች በመጠቀም የአውሮፓ ሕብረት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የጋራ ተጠቃሚነት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል አስተማማኝና ተዓማኒነት ያለው ወዳጅነት የጋራ ዕድገትን በሚያስቀጥል መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት እየገነቡ ከሚገኙ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካና ለአጠቃላይ አህጉሪቱ መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ሕብረቱ የኢትዮጵያን የብልፅግና ግስጋሴ በመደገፍ የልማት አጋርነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በገጠር የኃይል ልማት ተደራሽነት ላይ የአውሮፓ ሕብረት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በቀጣይም ሕብረቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኑን አረጋግጠው፤ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት መፂኢ ዕድል ለአውሮፓ አስፈላጊ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.