ኢትዮጵያና ባንግላዲሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሊሉር ራህማን (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት የትብብር መስኮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን አስረድተዋል፡፡
የባንግላዲሽ ኩባንያዎች መንግሥት ትኩረት በሰጠባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በታዳሽ ኃይል ማመንጫ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በፋርማሲና ሕክምና ቁሳቁስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሠማሩ ጠይቀዋል።
ካሊሉር ራህማን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት የትብብር ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሚኒስትሮቹ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በኢኮኖሚ ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡