Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት አገልግሎቶች ወደ ሕዝቡ እንዲጠጉ የማድረግ እድልን ይፈጥራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ሕዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መሄድ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ራሱ ወደ ሕዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጀምረውልናል ብለዋል።

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ሕዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መሄድ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ራሱ ወደ ሕዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል ሲሉም አስረድተዋል።

በአውቶቡሱ ላይ የአገልግሎት መስጫ ሥራ፣ የኃይል አማራጭ ሥራ (ከፀሓይ ብርሃን)፣ ፈጣን የኔትወርክ አማራጭን (MPLS = Multi Protocol Label Switching) በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ተደርጓል፣ የካሜራ ገጠማ እና የኮንፊግሬሽን ሥራ ተጠናቅቋል፣ የአገልግሎት መስጫ መሠረታዊ ግብዓቶች ተሟልቶ፣ የሙከራ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ ተደርጓል ሲሉም ጠቅሰዋል።

ከቴክኖሎጂ ዝግጅት አንፃር ወጪን የሚቆጥብ (በየማዕከላቱ የዳታ ማዕከል ግንባታን የሚያስቀር)፣ የአገልግሎት ጥራት እና ወጥነትን የሚያረጋግጥ፣ በሁሉም ማዕከላት ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የUnified Infrastructure Model ተግባራዊ ማድረግ መቻላችንን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው ብለዋል።

የተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የአዲስ መሶብ አገልግሎትን በተሟላ ደረጃ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው÷ ሕዝብ ባለበት ቦታ ሆኖ አገልግሎት እንዲያገኝ እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት የተጀመሩ አገልግሎቶችም የገቢ አገልግሎት (አዲስ ቲን ማውጣት)፣ የንግድ አገልግሎት (ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ)፣ የጤና (ለመንጃ ፈቃድ አካላዊ የጤና ምርመራ)፣ የሲቪል ምዝገባ (የመታወቂያ ዕድሳት እና ልደት)፣ የአሽከረካሪ ተሽከርካሪ (የመንጃ ፈቃድ እና የቦሎ ዕድሳት) መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የኢትዮ ፖስታ (የመንገድ ፈንድ ክፍያ)፣ የብሔራዊ መታወቂያ (አዲስ ምዝገባና የመረጃ እርማት) እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ቅድመ ክፍያ) የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው ብለዋል።

በከተማችን ብሎም በሀገራችን ለዘመናት የአገልግሎት ዘርፉን ለመለወጥ ሳይቻል ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትቦ የኖረ ቢሆንም መንግስት ቃል በገባው መሰረት ችግሩን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የሚለውጥ ‘የመሶብ’ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር ለተገልጋዩ ታላቅ ሽግግር እና እፎይታን ይዞ መጥቷልም ነው ያሉት።

ለሕዝባችን የምናቀርበው ባዶ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የገባነውን ቃል ሁሌ በታማኝነት በተግባር ተከታታይነት ያለውን የማያቋርጥ ተግባር እያከናወንን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.