Fana: At a Speed of Life!

በዓለም አቀፍ መድረኮች የባሕር በር ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ መድረኮችና የሁለትዮሽ ግንኙነት የኢትዮጵያ አንኳር ስትራቴጂካዊ አጀንዳ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።

የ2018 በጀት ዓመት ሶስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

መድረኩን አስመልክቶ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ÷ የለውጡ መንግሥት ሥራ ከጀመረ ወዲህ ባለው እንቅስቃሴ የተገኙ የዲፕሎማሲ ውጤቶች በመድረኩ ጠቅለል ተደርገው መታየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በዓለም አቀፍ መድረኮችና የሁለትዮሽ ግንኙነት የኢትዮጵያ አንኳር ስትራቴጂካዊ አጀንዳ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

አጀንዳውንም የተለያዩ አካላት እያወቁትና እየተገነዘቡት በጋራ መፍትሄ መፈለግ አለብን ወደሚል እሳቤ እየመጡ መሆኑ አንዱ ትልቅ ድል ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ በሆነ መንገድ ግንባታውና የውሃ ሙሌቱ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባቱና ይህ እንዳይሆን ለማድረግ የነበሩ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን መቋቋም ሌላኛው የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ የብሪክስ ፕላስ ሙሉ አባል ሀገር ሆና መመረጧና ተሳትፎ ማድረግ መጀመሯ ባለፉት ዓመታት የተገኘ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለኢንቨስትመንት፣ ለኢኮኖሚ አጋርነትና ለትብብር ተፈላጊ ሀገር እየሆነች መምጣቷ ብዙ የቅርብም የሩቅም ሀገራት ኢትዮጵያን ለትብብር እየፈለጉ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት የሚያደርጉበት የወዳጅነት አድማስ እየሰፋ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም በሚታይ ሁኔታ በጉብኝት ልውውጦች፣ በሚደረጉ ስምምነቶችና በተለያየ መልክ በሚገለጽ ሁኔታ ትብብርና ወዳጅነት እየሰፋ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲና ግንኙነትም የኢትዮጵያን ተጽዕኖ የሚጨምሩ የተለያዩ ስኬቶችና ድሎች መገኘታቸው ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውሳኔ ሰጪ አካላት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በከፍተኛ ድምጽ የተመረጠች አባል መሆኗን አንስተዋል።

የዲፕሎማሲ ውጤቶች የሚገኙት በዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ በሚደረግ እንቅስቃሴ ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ አጠቃላይ ሀገሪቷ በሚኖራት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ተቋማት ባላቸው ጥንካሬና በተገኙበት ደረጃ እንደሚመረኮዝ አስረድተዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ከፖሊሲ ሰነዶችና ንግግር አልፎ በተጨባጭ የተከወኑ ስራዎች በብዙ መልኩ መሠራታቸው ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን የሚመርጧት እንድትሆን አስችሏታልም ነው ያሉት።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.