ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ ለአየር ትራንስፖርት ዕድገት…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ የአየር ትራንስፖርት ዕድገትን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋል አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ 1412/18 መርምሮ አጽድቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ እንዳመለከተው÷ ከ21 ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ ተቋሙ የአቪዬሽን ደኅንነት ሥራዎችን በበላይነት ለመምራት እና ለማስተባበር የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ከስያሜው አንስቶ በግልፅ ያካተተ ነው።
የሀገራችንን የአየር ትራንስፖርት ዕድገት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያግዛል ያለው አገልግሎቱ÷ የአቪዬሽን ደኅንነትን ለማጠናከር ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ የመጀመሪያው የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን አመላክቷል።
በዚህም ነባሩ አዋጅ ኢንዱስትሪውን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ተግዳሮት ሆኖ ከመቆየቱም በላይ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ተቀጽላ 17 ስታንዳርዶችን ሳያካትት መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተሰጠውን የአቪዬሽን ደኅንነትን የማረጋገጥ ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት ከመወጣት አንፃር የጥራትና የቁጥጥር ስራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ የሚያስችሉ ሕጎችን መያዙ ተመላክቷል፡፡
አገልግሎቱ በአቪዬሽን ደኅንነት ረገድ ላስቀመጠው ራዕይ እና ስትራቴጂክ ግብ ስኬት መሰረት የሚጥል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ከቴክኖሎጂ አንፃር ኢንዱስትሪውን ለማዘመን አስፈላጊ የሆኑ ባለድርሻ አካላትን በኮሚቴነት መጨመሩ፣ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ስታንዳርዶችን በአዲስ መልክ ማካተቱ፣ የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እገዛ የሚያደርግ መሆኑና ከኢንዱስትሪው ፈጣን እድገት ጎን ለጎን ለመጓዝ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የሕግ ድጋፍ መስጠቱ በፋይዳነት የሚጠቀሱ መሆኑ በመረጃው ተገልጿል፡፡
የተሻሻለው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ ቁጥር 1412/18 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ አመልክቷል፡፡