Fana: At a Speed of Life!

ድርብ ኃላፊነት …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር ከገቡ ጉዳዮች መካከል ዲጂታል ቴክኖሎጂ አንዱና ዋነኛው ነው።

በተለይም ከዚህ ቀደም ያልተሰራበት እና የመጪው ዘመን ወሳኝ ትኩረት የሆነው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷ ሁሉም የሚረዳው ሀቅ ሆኗል።

‘የአርፍዶ ደራሽነት ምንዳን በመተው የቀድሞ ደራሽነት ምንዳን መቋደስ’ በሚል መርህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር የተተገበረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ስራ እመርታዊ ጉዞ ላይ ይገኛል።

ይህንን የተመለከተው የአፍሪካ ሕብረት ለዘርፉ ያለውን ቁርጠኝነት በማሳየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ አድርጎ ሾሟቸዋል።

በመሪነታቸውም ለአፍሪካ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት ዘመኑን የሚዋጅ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መረጃ የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር በፍጥነት እያደገ የመጣ ሲሆን ከአህጉሪቱ ጠቅላላ ምርት 9 በመቶውን የሚሸፍነው ይህ ዘርፍ ነው፡፡

በአህጉሪቱ ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ የኢንተርኔት አጠቃቀም 21 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ሲያሳይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች በዘርፉ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ አዲስ ክስተት የሆነው ሰው ሰራሽ አስተውሎት በተመሳሳይ በፍጥነት እያደገ የመጣ ሲሆን፤ በግብርና፣ ትምህርት እና ጤና ዘርፎች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለማሳደግ በማለም በፈረንጆቹ 2025 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደ ጉባኤ የ60 ቢሊየን ዶላር ፈንድ ይፋ ተደርጎ ወደ ተግባር ገብቷል።

በአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣበት በዚህ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው መሾም የህብረቱን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ሹመቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርፉን በመምራት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን በማስፋፋት ላመጡት የላቀ ውጤት እውቅና ከመስጠት ባለፈ አህጉሩ በዘርፉ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ያደረጉት አመራር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነትና ለአሳታፊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

ስልታዊ በሆነ መልኩ የቴክኖሎጂ ነጻነትን እና ዐቅምን ለመገንባት የሚያደርጉት ተከታታይ ቅስቀሳ፣ አህጉሩ በኃላፊነትና በፍትሐዊነት በታጀበ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተመላክቷል።

የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.