ፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ ያለው አባተ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ አምባሳደር ያለው አባተ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ተፈጽሟል።
በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
ከአባታቸው አቶ አባተ ረታ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ተዋበች ፋንታሁን በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር በራያ እና ቆቦ አውራጃ ቆቦ ወረዳ ጉብዬ ከተማ መጋቢት 10 ቀን 1946 ዓ.ም የተወለዱት አምባሳደር ያለው አባተ÷ በአማራ ክልል የክልሉ አፈ ጉባኤነትን ጨምሮ በተለያዩ ቢሮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሦስት ዓመታት በአፈ ጉባኤነት የሰሩ ሲሆን÷ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸውም ተመላክቷል።
አምባሳደር ያለው አባተ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።