Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ7 ቢሊየን 670 ሚሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ተችሏል አለ የከተማ አስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ።

የቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት በፍርድ ቤት ክርክር ከተደረገባቸው 5 ሺህ 30 የፍትሕብሔር መዝገቦች ውስጥ 2 ሺህ 249 ውሳኔ አግኝተዋል።

ውሳኔ ካገኙት መካከል 2 ሺህ 88 መዝገቦችን ለመንግስት በማስወሰን 7 ቢሊየን 670 ሚሊየን 637 ሺህ 854 ብር እንዲሁም 154 ቤቶች፣ 49 መስሪያ ቦታ ሼዶች እና 221 ነጥብ 34 ሄክታር መሬት የመንግስት እና ሕዝብ ጥቅም ማስጠበቅ መቻሉን አስረድተዋል።

በፍትሐብሔር ጉዳዮች የሚሰጥ ፍርድ ማስፈፀም በተመለከተ በፍርድ ቤት አፈጻጸም ከተከፈተባቸው 93 መዝገቦች 89ኙን፣ 784 የሁከት ይወገድልኝ መዝገቦች፣ 285 እግዶች፣ 84 የመንግስት ፕሮጀክቶች እና 49 በሕገ ወጥ መንገድ በተያዙ የመስሪያ ቦታ ሼዶች በጥቅሉ 1 ሺህ 295 መዝገቦች ውስጥ 1 ሺህ 291 ላይ ለከተማ አስተዳደሩ ማስፈጸም መቻሉን ተናግረዋል።

በግል ቆሞ የመከራከር ዐቅም ለሌላቸው አረጋዊያን፣ ሴቶችና ሌሎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 43 የሕብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

በግል አቤቱታ ምርመራ ተጣርቶ ከቀረቡ 7 ሺህ 722 የወንጀል ምርመራ መዛግብት ውስጥ 6 ሺህ 755 መዝገቦች በእርቅ እልባት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በጽሑፍ ለ216፣ በቃል ለ1 ሺህ 143 የሕግ አስተያየትና ምክር ጥያቄዎች ላቀረቡ ግለሰቦች በሙሉ እንዲሁም ከተቋማት ለቀረቡ 476 የውል አስተያየት እና 378 የውል ይረቀቅልን ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን አቶ ተክሌ አብራርተዋል፡፡

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ነባር ሕጎች የማሻሻል እና 45 አዳዲስ የሕግ ረቂቆች ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.