የጋምቤላ ክልል 5 ሺህ 535 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አስገባ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከጋምቤላ ክልል ባለፉት 9 ወራት 5 ሺህ 535 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል አለ የክልሉ ማዕድን ቢሮ፡፡
የቢሮው የ2018 በጀት ዓመት 9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በተገኙበት ቀርቧል፡፡
ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የወርቅ ማዕድን ሀብት እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው።
በክልሉ ያለውን ሰፊ የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማት በማዘመንና ከብክነት በመታደግ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በባህላዊ፣ በልዩ አነስተኛና በወርቅ አምራች ኩባንያ የተመረተ 5 ሺህ 535 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን አመልክተዋል።
በዘርፉ የታየው አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ከ1 ሺህ 278 ኪሎ ግራም በላይ ብልጫ እንዳለው መጠቆማቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡