Fana: At a Speed of Life!

ኤ አይን በሚገባ የተረዳና ለበጎ አላማ የሚጠቀም የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ቴክኖሎጂን በሚገባ የተረዳና ለበጎ አላማ የሚጠቀም የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው አሉ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፡፡

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ከእሑድ ኤ አይ ስቱዲዮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኤ አይ ሙዚቃ ውድድር ተካሂዷል፡፡

ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደሉት÷ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ዘርፍ ያላትን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አሁን ላይ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ችግሮች የሚፈቱበት ቁልፍ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ኤ አይ የሰው ልጅን የማሰብ፣ የመገንዘብ፣ የማመዛዘን፣ የማቀድ፣ የመማርና ቋንቋን የመረዳት አቅምን በማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን ያስችላል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በጥበብና መዝናኛው ዘርፍ ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማጠናከር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አዲስ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ለችግሮች አዲስ የመፍትሄ ሃሳብ ማመላከቻ መንገድ በመሆን በዘርፉ ይዘቶችን በፍጥነት ለማዘጋጀት አማራጭ ሃሳብ ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

ተቋማቸው ኤ አይ ቴክኖሎጂን በሚገባ የተረዳ እና ለበጎ አላማ የሚጠቀም የሰው ሃይል ለማፍራት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የኤ አይ ሙዚቃ ውድድሩ የዚሁ ሥራ አካል መሆኑን ጠቁመው ÷ ይህም ቴክኖሎጂው በጥበብ ዘርፍ ያለውን አቅም ከማሳየት ባለፈ በኢትዮጵያ ታሪክ የቴክኖሎጂና ጥበብን ጥምረት መግለጽ ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው የኤ አይ ሙዚቃ ውድድር በጎ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጠራ ትግበራን በማበረታታት ወጣቶች ቴክኖሎጂውን በሃላፊነትና በሥነ ምግባር እንዲጠቀሙ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውድድሩ በሙዚቃ ባለሙያዎች እና በዘርፉ ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የይዘት ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች መኖራቸውን መረዳት እንደተቻለ ጠቁመው ÷ በሒደቱ የተገኘው ውጤት አበረታች እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.