Fana: At a Speed of Life!

የዲግሪ ሰርተፊኬት ህትመት በአንድ ማዕከል ብቻ ሊከናወን ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የዲግሪ ሰርተፊኬት ህትመት በአንድ ማዕከል ብቻ ሊከናወን ነው አለ ትምህርት ሚኒስቴር።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደርና መሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ አሰራሩ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመከላከል ያለመ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨረታ ባሸነፈ ድርጅት በኩል የተማሪዎችን የትምህርት ማስረጃ የሚያሳትሙበት አሰራር ለሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አጋላጭ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የመንግሥት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎቻቸውን ዲግሪ በአንድ ማዕከል ብቻ እንዲያሳትሙ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

አዲሱ ዲግሪ ታትሞ እስኪደርስ ድረስ ትምህርት ሚኒስቴር ዲግሪ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚጽፍ ገልጸው፤ ህትመቱ በዚህ ዓመት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

የሚታተመው ሰርተፊኬት የደህንነት መለያ መስፈርቶችን እንደሚያሟላ ገልጸው፤ ልዩ መለያ ኮድ(QR Code) እና ሴሪያል ቁጥርን ጨምሮ ሌሎች መለያዎችን ያካተት እንደሚሆን ገልጸዋል።

በ2017 ዓ.ም የተመረቁ ተማሪዎችን ጨምሮ ከዚህ በኋላ የሚመረቁትም ሙሉ በሙሉ በአዲሱ ስርዓት መሰረት በአንድ ማዕከል የሚታተመውን ዲግሪ ብቻ እንዲወስዱ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከ2017 ዓ.ም በፊት ተመርቀው ነገር ግን ዲግሪያቸውን ያልወሰዱ ተማሪዎች በአዲሱ አሰራር ብቻ እንደሚስተናገዱ አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው ጊዜያዊ የትምህርት ማስረጃ (Temporary Degree) አሰጣጥ በነበረበት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ከ160 በላይ በሚሆኑ የፌዴራል ተቋማት ላይ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጥራት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አንስተው፤ በቀጣይ በክልሎች እና በግሉ ዘርፍ የማጥራት ስራው እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.