ተጠርጣሪዎች የተሰወረ ታክስን እንዲከፍሉ ማድረግ ተችሏል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታክስ የሰወሩ ተጠርጣሪዎችን በወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር የተሰወረው ታክስ እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል አሉ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ።
ዋና ዳይሬክተሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በኩል የታክስ ስወራን የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው።
የታክስ ስወራ ጥርጣሬ ሲያጋጥም ለታክስ ሰብሳቢ ተቋማት በማሳወቅ ምርመራ እንደሚካሄድ አንስተው፤ በዚህም ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የተሰወረ ታክስ እንዲመለስ መደረጉን አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከታክስ ስወራ ጋር የተያያዙ ክትትሎች እና ምርመራዎች በተጠረጠሩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የባንክ ሒሳቦች ላይ ተደርገዋል ብለዋል።
በታክስ ስወራ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ከ6 ሺህ በላይ የባንክ ሒሳቦች ላይ ምርመራ መደረጉን አስረድተዋል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት ከታክስ ስወራ ጋር ተያይዞ ለክልል እና ለፌደራል ተቋማት 129 የደህንነት ሪፖርት መላኩን ገልጸዋል።
969 ተጠርጣሪዎች በቀጥታ የተሰወረውን ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።
ታክስ የሰወሩ ተጠርጣሪዎችን ከፍትህ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በወንጀል ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ መቀጠሉንም አስረድተዋል።
በታሪክ አዱኛ