ዜጎች በምርጫ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ዴሞክራሲን ያጎለብታል – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕግ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ዜጎች በምርጫ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ዴሞክራሲን ያጎለብታል አሉ።
የመንግሥት ምስረታ በምርጫ ሲሆን የሀገርን እድገት በሁለንተናዊ መልኩ ለማስጠበቅ ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ሀገራት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የዜጎቻቸውን ንቁ ተሳትፎ በማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ችለዋል ብለዋል።
በምርጫ የጸና መንግሥት በዓለም አቀፍ መድረኮች ከሚኖረው ቅቡልነት በተጨማሪ ሰላምን ለማጽናት እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ተሻለ ሰበሮ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ የሀገር ውስጥ ጥንካሬ በተገቢ ሁኔታ ከተገነባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ያስችላል።
ይህም አይበገሬነትን፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን እንዲሁም የማህበረሰባዊ አንድነትን በማቀናጀት የማይበገር ኃይል ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።
አሁን ላይ ወታደራዊ አቅም በቴክኖሎጂና በሳይንስ መዘመኑ፣ የኢኮኖሚ እድገቱ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ እየተስተዋለ የሚገኘው ጥንካሬ የኢትዮጵያ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲሰማ ማድረጉን አንስተዋል።
የሥራ አመራር አማካሪ አቶ ጌትዬ ትርፌ በበኩላቸው፤ የዜጎች የምርጫ ሂደት ተሳትፎ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ያደርጋል ብለዋል።
በዚህም በምርጫ የጸና መንግሥት እንዲኖር ዜጎች የያዙት የምርጫ ካርድ ዋጋ በቀላል የሚታይ አለመሆኑን አክለዋል።
ዴሞክራሲያዊ እድገት ላይ የደረሱ ሀገራት የህዝባቸውን ተሳትፎ ማሳደግ በመቻላቸው አሁን ላሉበት ደረጃ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል ያሉት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ኤቢሶ ናቸው።
በዮናስ ጌትነት