ምርጫና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ
አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተገቢውን የዴሞክራሲ ተሳትፎና ውክልና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀችው የዓለም ዓቀፉ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን፤ አካል ጉዳተኞች በፖለቲካው መስክ በነፃነት የመሳተፍ፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ በሚመርጧቸው ተወካዮች የመተዳደርና የመወከል መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡
እነኚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በፖለቲካና እና በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች እንዲሳተፉ በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 29 ስር ተደንግጓል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የምርጫ አዋጃችን ቁ. 1162/2011 በምርጫ ወቅት የኮንቬንሽኑ አንኳር ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
አዋጁ የአካል ጉዳተኞች የጉዳት ዓይነት በመራጮች መዝገብ ላይ እንዲገለፅ ከማድረግ አንስቶ ለዕጩነት ለመቅረብ የሚያስፈልገው የድጋፍ ፊርማ ብዛት ከሌሎች ዕጩዎች ያነሰ እንዲሆን፤ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከፍ እንዲል እነርሱን በአባልነት፣ በዕጩነት እና በአመራርነት ለሚያሳትፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበትን የማበረታቻ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
ስለሆነም የእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታ በተገቢው ተጠንቶ የመራጮች ትምህርት እንዲያገኙ፣ በመራጭነት/ተመራጭነት እንዲመዘገቡ እና እንዲመርጡ ይደረጋል፡፡
በዚህ ረገድ ለአካል ጉዳተኞች የምርጫ አሰራሮች ምቹ እንዲሆኑ፣ ቁሳቁሶችና የምርጫ ስፍራዎች ለአካል ጉዳተኞች ተስማሚነት እንዲኖራቸው፣ ድምጻቸውን በነፃነትና በምስጢር የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ እርዳታ የሚሹ ከሆነ በሚመርጡት ሰው እንዲታገዙ፣ ተመርጠው በማናቸውም ደረጃ የማገልገል ዕድል እንዲኖራቸው እና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ድጋፎች እንዲደረግላቸው መብት አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ትመርጣለች!