Fana: At a Speed of Life!

የአትሌት የብርጓል መለሰ ሥርዓተ ቀብር በነገው ዕለት ይፈጸማል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ መድረክ ኢትዮጵያን በክብር ያስጠራችው ጀግና አትሌት የብርጓል መለሰ ሥርዓተ ቀብር በነገው ዕለት ይፈጸማል።

ሥርዓተ ቀብሩ ነገ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አትሌት የብርጓል መለሰ በረጅም ርቀት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ስታስጠራ ቆይታለች፡፡

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀምሮ በበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ በመካፈል ስኬታማ ጊዜያትን በአትሌቲክሱ አሳልፋለች፡፡

አትሌቷ በፈረንጆቹ 2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሀገሯን ወክላ በግማሽ ማራቶን ውድድር የነሃስ ሜዳልያ ማሸነፏ ይታወሳል።

በዚያው ዓመት በቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳልያ ባለቤት የነበረች ሲሆን፤ በሻንጋይ፣ ፕራግ እና ሂውስተን ማራቶኖች በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

በፓሪስ ግማሽ ማራቶን ውድድር ሁለት ጊዜ ድል የተቀዳጀች ሲሆን፥ በሊዝበን ግማሽ ማራቶን ውድድርም በቀዳሚነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም፡፡

በቀጣይ በካናዳ በሚካሄደው የኦታዋ ማራቶን በመሳተፍ ሀገሯን ለማስጠራት ሕልም የነበራት አትሌት የብርጓል መለሰ ትናንት ማለዳ በመደበኛ የልምምድ መርሐ ግብሯ ላይ እያለች በተወለደች በ36 ዓመቷ በድንገት ህይወቷ ማለፉ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.