በአዲስ አበባ ውበት የተደመመው ዲላን ፔጅ…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 19 ነጥብ 3 ሚሊየን የቲክቶክ ገጽ ተከታይ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪው ዲላን ፔጅ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡
ዲላን ፔጅ ቲክቶክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች በፈጣን ዜና አቀራረብ እና የተለያዩ መረጃዎችን በማጋራት ይታወቃል፡፡
ዲላን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ደስተኛ መሆኑን እና የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እንዳስደመመው በቲክቶክ ገጹ ባጋራው መልዕክት ገልጿል።
ትንታኔዎችንና የመረጃ ይዘቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ዲላን በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ወቅት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረውን ታላቅ ሕዝባዊ ደስታና የአንድነት ስሜት በተመለከተ መረጃዎችን ማጋራቱ ይታወሳል፡፡
“በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀይረው የአፍሪካ የብርሃን ተስፋ” በሚል ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
የዲላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የቱሪዝም ዘርፉን በማስተዋወቅ እንዲሁም ለዲጂታል ዲፕሎማሲው ስኬት እና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማሳየት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል፡፡
ዲላን ፔጅ በቆይታው በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም ሥፍራዎችን በመጎብኝት ለዓለም ያጋራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ በመገኘት የከተማዋን ውበት እና የኢትዮጵያን የእድገት ጉዞ ለዓለም ማጋራታቸው ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ አየለ