የዘመናዊ ሳይንስ መሰረት የሆነው ሀገር በቀል ዕውቀት …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል ዕውቀት ለዘመናዊ ሳይንስ ምርምር እና ወደ ዘመናዊነት ለመሻገሪያ አንዱ መንገድ መሆኑ ተመላከተ።
የመጀመሪያው ከተማ አቀፍ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ በዘርፉ ተመራማሪዎች የመነሻ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ማልማት፣ መጠበቅ፣ መሰነድ፣ ማስተዋወቅና ማስተላለፍ ከሁሉም አካላት እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
“ህይወታችንን ለመለወጥ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን እንዴት እንጠቀም ?” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ጌትነት ፈለቀ (ዶ/ር) ዝርዝር ሀሳቦችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።
በስሩ በርካታ ሀገራዊ ዕሴትና ባህሎችን የያዘው ሀገር በቀል ዕውቀት፤ ለዘመናዊ ሳይንስ ምርምርና ወደ ዘመናዊነት መሻገሪያ አንዱ መንገድ መሆኑ ተብራርቷል።
ማህበረሰባዊ ህክምና፣ የህግና የፍትህ ሥርዓት፣ የአመጋገብና የአለባበስ ስርዓት እንዲሁም ሌሎችም ነባር ማንነቶችን ለማስጠበቅ እና ለአካባቢያዊ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ ለመስጠት ጠቃሚ መሆኑ ተመላክቷል።
ሀገር በቀል ዕውቀትን ከቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ ለፈጠራ ሥራና ለኢኮኖሚ ዕድገት መጠቀም እንደሚገባም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ