Fana: At a Speed of Life!

የኖርዌይ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንፈልጋለን አሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኖርዌይ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢ ሞቢሊቲ እና በአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንፈልጋለን አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከኖርዌይ አምባሳደር ስታይን ክሪስተንሰን ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ኖርዌይ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በመድረኩ በተለይም በአረንጓዴ ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በኢ ሞቢሊቲ (በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች) እና በዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ላይ በትብብር ለመስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ መንግሥት የኢንቨስትመንት ምሕዳሩን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም አዳዲስ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ክፍት ማድረግ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ የሚረዱ ተቋማትን ማቋቋም እና ምቹ የሆኑ የኢንቨስትመንት ሕጎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ይህም ግልጽና ተገማች የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር እንዳስቻለ ማስረዳታቸውን ኮሚሽኑ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

መንግሥት በተለይ በኢሞቢሊቲ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎች ያወጣ መሆኑን ጠቅሰው ÷ በዘርፉ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኖርዌይ ባለሃብቶች ይህንን ዕድል ተጠቅመው በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስታይን ክሪስተንሰን በበኩላቸው÷ የኖርዌይ ባለሃብቶች በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በታዳሽ ኃይል ልማት እና በኢ ሞቢሊቲ ዘርፍ ያላቸውን ሰፊ ልምድ በመጠቀም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.