በኦሮሚያ ክልል የ2 ነጥብ 8 ቢሊየን የቡና ችግኝ ተከላ ዘመቻ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የ2 ነጥብ 8 ቢሊየን የቡና ችግኝ ተከላ ዘመቻ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በዚህም በጅማ ዞን በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ700 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ በቡና ልማት ኢኒሼቲቭ በግብርና ምርምር የተመረጡና በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎች በስፋት እየቀረቡ ይገኛሉ።
በክልሉ በቡና ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ያህሉ ምርት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ተክሎች በአዲስ ዝርያ እየተተኩ እንደሆነ አስረድተዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፥ በዞኑ አሁን ላይ የቡና መሬት ከ360 ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የዘንድሮው ዘመቻ በክልሉ ያለውን የቡና መሬት ስፋት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።
በሁሴን ከድር