የሀገር መከላከያ ሰራዊት በላቀ ሙያዊ ብቃት ተልዕኮውን እየተወጣ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት በላቀ ሙያዊ ብቃት ተልዕኮውን እየተወጣ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡
የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ27ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን እጩ መኮንኖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ሀገርን ለማፍረስ ጥረት ቢያደርጉም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አፍረው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡
የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ በመቀበል የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ በተወሰዱ ርምጃዎች ድል መቀዳጀት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ተመራቂ እጩ መኮንኖች የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ የጠላት ምኞት እንዲመክንና የሕዝቡ ሰላምና ልማት እንዲጎለብት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ተመራቂዎች በት/ቤቱ የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ካላቸው ልምድ ጋር በማቀናጀት የሰራዊቱን የተልዕኮ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ባንዳዎችን በማፅዳትና የሀገርን ሰላም በማፅናት ረገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የጀግንነት ታሪክ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ት/ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫንጮ በበኩላቸው፥ ተመራቂ እጩ መኮንኖቹ የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ድል ማድረግ የሚያስችል አቅም መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተስፋዬ ኃይሉ