በጋምቤላ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እየተሻሻለ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን ከማጠናከር ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሻሻሉ ነው አለ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድሪው ቱት እንዳሉት÷ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
አርሶ አደሮቹ በተለይም በአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ብርቱካን ልማት ላይ በማተኮር ለገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በማቅረብ የቤተሰብ ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፍራፍሬና የአትክልት ልማት በአካባቢው የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን በማሻሻል የምግብ ዋስትና ግብን ለማሳካት አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠልም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ምርትና ጥራት ያላቸው የአቮካዶ ችግኞች እየተሰራጩ እንደሚገኙ መጥቀሳቸውን ቢሮው ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በዘንድሮው ክረምት ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ጋር በማቀናጀት አቮካዶን ጨምሮ ከ8 ሚሊየን በላይ የፍራፍሬና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።