Fana: At a Speed of Life!

ንቅናቄው ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የኢኮኖሚ ትግል ምዕራፍ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

በአዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የኢኮኖሚ ትግል ምዕራፍ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሌሎች ሀገራት ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የገነባ ሀገር ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ ነው ሊባል አይችልም።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የራስን አቅም በመጠቀም የራስን ምርት ማምረት በሚል መርሕ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ÷ ንቅናቄው ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የኢኮኖሚ ትግል ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረውን ፍጆታን ብቻ መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ በመቀየር አሁን ላይ ሀገሪቱ በራሷ ልጆችና ግብዓት የራሷን ምርት በማምረት እንድትጠቀም ንቅናቄው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታች ነው፤ ይሁን እንጂ የኢኮኖሚ ፍትሐዊነትንና የብዙዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ በክልሉ እየተመረቱ ያሉ ምርቶች በዋናነት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩና ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የክልሉን ሁለገብ አቅም በመጠቀም በሁሉም ዘርፍ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ትልቅ ለውጥ ቢመዘገብም የኃይል አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት ችግር እና የፋይናንስ እጥረት አሁንም የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆነው መቀጠላቸው በመድረኩ ተመላክቷል።

በአለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.