Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ናይጀሪያ ፍርደኞችን ለመለዋወጥ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ቲሞቲዎስ (ዶ/ር) ከናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ቢያንካ ኦዱሜግዉ-ኦጁክው ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለውና ከፈረንጆቹ 1960ዎቹ ጀምሮ የዘለቀ ነው።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ ጉዳዮችና ጥቅሞች ላይ ቀጣይነት ያለው ቅንጅት እና ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

አምባሳደር ቢያንካ ኦዱሜግዉ-ኦጁክው በበኩላቸው ናይጄሪያ የሁለትዮሽ ትብብሩን ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው÷ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ እና የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግና የፍትህ ሚኒስትር ላቲፍ ኦላሱንካንሚ ፋግቤሚ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉ ፍርደኞችን የመለዋወጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የፍትህ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ በማጠናከር በዘርፉ ለሚደረገው የጋራ ስራ ጠቃሚ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ሁለቱ ወገኖች ዛሬ የተካሄደው ውይይት እና የተፈረመው ስምምነት በኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ መካከል ያለውን አጋርነትና ትብብር ይበልጥ እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.