የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት ለቀጣናው ሁለንተናዊ ዋስትና…
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ አቅዳ በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች፡፡
እቅዱን ለማሳካትም ትኩረቱን በተግባራዊ አፈጻጸም ላይ ያደረገ አዲስ ገቢር ነበብ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እይታ የተቃኘ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተከተለች ነው፡፡
በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች አማካኝነት የገበያ ውድድር እንዲሰፍንና የኢኮኖሚ አቅም እንዲጎለብት ተደርጓል።
የስንዴ ልማት፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጅማሮ፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኢትዮጵያ ታምርት፣የኮሪደር ልማት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያና ሌሎች ሥራዎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልዕልና ጅማሮ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላትን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በዘላቂነት ለማረጋገጥም የባሕር በር ተጠቃሚነትን ማሳካት ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካለው ልምምድና መርሕ ውጪ በታሪካዊ ስሕተቶች እና ጠላቶች በሸረቡት ፖለቲካዊ ሴራ የባሕር በር ተከልክላ መኖር አትችልም፡፡
ለሺህ ዓመታት የባሕር በር ባለቤት የነበረችው ሀገር በ30 ዓመታት አጭር ስሑት ትርክት ምክንያት ከባሕር በር እርቃ እንደማትቀጥልም እርግጥ ሆኗል፡፡
አሁን ላይ የባሕር በር ጉዳይ ከነበረበት የመሽኮርመም ፖለቲካ እና የመዘንጋት አዙሪት ወጥቶ የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ጉዳይን የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ማጠንጠኛ ማዕከል እንዲሆንና ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ ከማድረግ አንጻር የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 130 ሚሊየን ሕዝብ የያዘችው ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ድርሻ ሊኖራት ግድ ነው፤ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም ሲሉ ጽኑ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባሕር በር ተጠቃሚነትን በምክክርና ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ለማረጋገጥ የጀመረችው ጥረትም ዓለም አቀፍ እውቅና እየተቸረው ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው በተለይም ሽብርተኝነት ከመከላከልና የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በስኬት ከማከናወን አንጻር ጉልህ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡ ለዚህም የዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና አስፈላጊውን ወታደራዊ ግዳጅ መፈጸም የሚችል ግዙፍ መከላከያ ገንብታለች፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሀገር ዳርቻ አልፎ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የቆመ የታማኝነትና የጥንካሬ ተምሳሌት መሆኑም ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷም በቀጣናው ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ብሎም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን አፈጻጸም በእጅጉ ያሳድጋል፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የሀገርን ኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚወስን ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅምና የሕልውና ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው፡፡
በአንጻሩ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታት ኤርትራ ኢትዮጵያ ላቀረበችው የማይናወጥ የባሕር በር ጥያቄ በጎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አሉታዊ መንገድን የመረጠች ይመስላል፡፡
ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ብሄራዊ አጀንዳ የሆነው ፍትሃዊ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በታሪክ አጋጣሚ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለማራቅ የውስጥ ባንዳዎችን በማሰለፍ ጭምር የሸረቡትን ሴራና የተሳሳተ ስሌት ከመሰረቱ ለመናድ የተጀመረው ጥረት በርካታ ውጤቶችን እያስገኘ ነው፡፡
ለባሕር በር ጥያቄው ምላሽ ለማግኘትም ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ ያሳዩት የተደመረ ዕይታና ጽኑ አቋም ትልቅ እመርታ ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፡፡
ምክንቱም ጥያቄው ታሪካዊነትን ከመልክዓ ምድራዊነት፣ ሕጋዊነትን ደግሞ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያሰናሰለ ጠንካራና ምክንያታዊ መሠረት ያለው በመሆኑ ነው፡፡