Fana: At a Speed of Life!

ጠንክረው ከሰሩ የማይሳካ ነገር የለም – ከ60 ኮርሶች 47ቱን ‘A+’ ያስመዘገበችው ተመራቂ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀሰምኩት እውቀት በቀጣይ ተጨባጭ ሥራ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ አለች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከ60 ኮርሶች 47 ‘A+’ እና 13 ‘A’ በማስመዝገብ የተመረቀችው መሐንዲስ ሩት አባተ፡፡
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።
ከነዚህም መካከል የኤሌክትሪካል ፓወር ኤንድ ኮንትሮል ኢንጂነሪንግ ተመራቂዋ ሩት አባተ የዓመቱ ኮከብ ተማሪ በመሆን የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።
በከፍተኛ ውጤት የተመረቀችው ሩት ይህንን ስኬት ልታስመዘግብ የቻለችው ከመጀመሪያው ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ጀምሮ በትምህርቷ ላይ ሙሉ ትኩረት በማድረግ ጠንክራ በማጥናቷ መሆኑን ተናግራለች።
“ሙያው ለሴቶች ፈታኝ እንደሆነ ቢነገርም፤ እኔ ግን ይህንን አመለካከት በመስበር ለሌሎች ሴቶች አርአያ መሆን እንደምችል በተግባር ማሳየት ችያለሁ” ትላለች።
ላስመዘገበችው ስኬት ሁልጊዜ ከጎኗ በመሆን በሁሉም ረገድ ድጋፍ ለሚያደርጉላት ቤተሰቦቿ ምስጋና አቅርባለች።
መሐንዲስ ሩት በቀጣይ ትምህርቷን በማጠናከር የማስተርስ ዲግሪዋን የመቀጠል ትልቅ እቅድ እንዳላት ተናግራለች።
በትምህርት ገበታ ላይ የቀሰመችውን እውቀት በተግባር ወደ መሬት በማውረድ የሚታይና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.