Fana: At a Speed of Life!

የኢጋድ አባል ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የሳይበር ደህንነት ስጋትን ለመከላከል…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የሳይበር ደህንነት ስጋትን ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትብብር መስራት አለባቸው አለ፡፡

ኢጋድ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢጋድ ቀጣናዊ የሳይበር የተግባር ልምምድ ስልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የኢጋድ ተጠሪ አበባው ቢሆነኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሳይበር ደህንነት ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል ዘመኑን የዋጀ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሳይበር ደህንነት ሥጋት ዓለም አቀፍ የጋራ ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ከዚህ በመነሳትም የኢጋድ አባል ሀገራት በመተባበርና ተቋማዊ አሰራራቸውን በማጠናከር ቁልፍ መሠረተ ልማቶቻቸውን በጋራ መጠበቅ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡

አባል ሀገራቱ ድንበር ተሻጋሪ የሳይበር ደህንነት ስጋትን መከላከልና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ትብብር መፍጠር እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

ኢጋድ በቀጣናው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ለአባል ሀገራቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ስጋትን መከላከልና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዝግጅት እንደሚፈልግ ጠቁመው ለዚህም÷ አህጉራዊና ቀጣናዊ የሳይበር ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለአጀንዳ 2063 መሳካት ኃላፊነት እንዳለባት ሀገር ግቦችን እውን ለማድረግ ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠር አበክራ ትሰራለች ብለዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.