የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አላማችን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ነው አሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እና የኤርፖርትና የድንበር አስተዳደር ትራንፎርሜሽን ፕሮግራም ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን።
የኤርፖርት እና የድንበር አስተዳደር ትራንፎርሜሽን ፕሮግራም የምክክርና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ፕሮግራሙ እንደሀገር የሚያጋጥሙ የደህንነት ስጋቶችን በመረጃ አስደግፎ አስቀድሞ ለማወቅና ለመከላከል ጉልህ ሚና ያበረክታል።
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግና በቀጣይ የምታስተናግዳቸውን ግዙፍ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በስኬት ለመምራት እንደሚያግዝም አብራርተዋል።
ፕሮግራሙን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር ከ10 ተቋማት የተውጣጡ ብሔራዊ አስተባባሪና ቴክኒካል ኮሚቴዎችን ያቀፈ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተዋል፡፡
ለትግበራው ስኬታማነት የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች የተቀመሩበት ስትራቴጂካዊ ሰነድ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉን ነው የገለጹት፡፡
አይነታቸውንና ይዘታቸውን እየቀያየሩ የመጡ ግጭቶችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል ፕሮግራሙ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውና የኢትዮጵያን አህጉራዊና ቀጣናዊ አቅም ታሳቢ ያደረገ ሁለንተናዊ የደህንነት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
አሰራሩ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች በስፋት እንዲለሙ በማድረግ የሀገሪቱን የሳይበር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሞች በተሟላ ሁኔታ የሚያረጋግጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በመድረኩ የፌደራል ተቋማት ሃላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ከንቲባዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ