Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክር የመደማመጥ፣ የመግባባትና የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ፣ አካታችና ስልታዊ የምክክር ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ይህ ምዕራፍ ለዘመናት የዘለቁ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሕዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለመፍታት፣ በሰለጠነ የውይይት መድረክ ላይ የጋራ ብሔራዊ መግባባትን ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል ነው።

ለረጅም ጊዜ በውስጥ ሽኩቻዎችና በቅሬታዎች የተተበተበውን የፖለቲካ ባህል በመቀየር፣ አካታችነትንና ብሔራዊ መግባባትን የሉዓላዊነትና የብልጽግና ዋነኛ መሠረት የሚያደርግ ራዕይ ዛሬ በተጨባጭ እየተተገበረ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፣ ጠንካራ፣ ሉዓላዊና የተረጋጋ ሀገርን መገንባት የሚጠይቅ ታሪካዊ ግዴታ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃነት፣ የተለያዩ ባህሎችና የፖለቲካ አመለካከቶች ባሉባቸው ሀገራት ውስጥ፣ የአንድ ወገንን ሐሳብ ብቻ በመጫን መጓዝ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።

ስለዚህ የሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ ይታያል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው ስምንቱ ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎች፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ የኢትዮጵያውያን ድምፆች፣ ተስፋዎችና የወደፊት ራዕዮች ማንጸባረቂያ ናቸው።

የእነዚህ አጀንዳዎች ስኬታማነት ወደ ተግባር የመቀየር ሂደት የአንድ ወገን ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን፤ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን በጎና ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራንና ሌሎች ተቋማት ለዚህ ታሪካዊ ሂደት ስኬት የማይተካ ሚና አላቸው።

ይህ ሂደት በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በማጠናከር፣ ለመጪው ትውልድ በሰላም፣ በመተማመንና በመተባበር የሚኖርባትን ሀገር ለማስረከብ ትልቅ ታሪካዊ ዕድል ነው።

ይህንን ዕድል በብልህነት በመጠቀም የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ መወሰን ይገባናል።

በመሆኑም የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ለማደናቀፍ ከተቀመጡት አጀንዳዎች ውጭ በሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ሐሳቦች ፊት በጽናት መቆም፣ ለመደማመጥና ለመግባባት ቅድሚያ በመስጠት፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የራሳችንን አዎንታዊ አሻራ ልናሳርፍ ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.