የትውልድ ቅርስ እና የህልውና መሰረት…
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ይገኛል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ፍቱን ሆኗል፡፡
በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ሀገራዊ የችግኝ ተከላና የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ንቅናቄ በአካባቢ ጥበቃ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች በርካታ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጭምርም ችግኞችን በማጋራት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የአፍሪካ ምሳሌ በመሆን አረንጓዴ ዲፕሎማሲን እየገነባች ትገኛለች፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሀገሪቱ ያላትን የደን ሽፋን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።
ዛፎች የአየር ንብረት መዛባትን በመከላከል በካይ ጋዞችን አምቀው በመያዝ የአካባቢ ሙቀት እንዲስተካከል እና የአየር ንብረቱ ለኑሮ ምቹ እንዲሆን ያደርጋሉ።
በዝናብ እና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የሚመጣን የአፈር መሸርሸር በመከላከልም የመሬት ለምነትን ይጠብቃሉ።
እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎችን ማልማት ደግሞ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግም በላይ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለሀገር አቀፍ ወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ እስከ አሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች፡፡
በዚህም የደን ሽፋናችን ከነበረበት ከ17.2% ወደ 23.6% ከፍ ብሏል፡፡
ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር መጠን ከ1.9 ቢሊዮን ቶን ወደ 208 ሚሊዮን ቶን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ይህ ለውጥ በተለይ ግድቦችን ከደለል አደጋ ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ አድርጓል።
በመላ ሀገሪቱ ከ197 ሺህ በላይ የተፋሰስ ልማት ማኅበረሰቦች ተቋቁመው የውሃ ምንጮች እንዲያንሰራሩና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር አድርገዋል።
ችግኞችን በማዘጋጀት፣ በመትከል እና በመንከባከብ ሂደት ውስጥ ለ2.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
ደኖች በመልማታቸው ምክንያት ቀድሞ ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳት እና የተለያዩ አእዋፋት ወደ ቀደመ መኖሪያቸው መመለስ ጀምረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ በሀገር አቀፍ ደረጃ የችግኝ ጣቢያዎች ቁጥር ከ40 ሺህ ወደ 120 ሺህ በማደጉ የአካባቢውን የችግኝ አቅርቦት ሰንሰለት አጠናክሮታል።
መርሃ ግብሩ የዜጎችን ተሳትፎና አንድነት በማጠናከር፣ በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በፈቃደኝነት በጋራ በመሳተፍ ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ግንዛቤና ማኅበራዊ ትስስር እንዲያሳድጉ አድርጓል፡፡
ችግኝ መትከል የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ ዋናው ኃላፊነት የተተከለውን ማደጉን ማረጋገጥ ነው።
የችግኞችን የጽድቀት መጠን ለመከታተል መንግሥት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ተግብሯል፤ ለእያንዳንዱ ችግኝ መለያ ቁጥር የመስጠት ሥራዎችንም እያከናወነ ይገኛል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋም የተከላቸውን ችግኞች በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ፣ ውብ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ አለበት።