Fana: At a Speed of Life!

ኪነ-ጥበብ ለሀገር …

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ስሜትን፣ እሳቤን፣ ፍልስፍን እና እውነታን በውብ ድምፅ፣ ምስል፣ ቃላት ወይም እንቅስቃሴ መግለጫ የሆነው ኪነ-ጥበብ የየዘመኑን ባህል፡ ታሪክ፡ አኗኗርና ፖለቲካዊ እውነታዎች ቀጣይ ትውልድ ከሚረዳባቸውና ትምህርት ከሚወስድባቸው መንገዶች ቀዳሚው ነው፡፡
ስነ-ጽሁፍ፣ ቲያትር፣ ሙዚቃ፣ ስዕል እና ሌሎችም የኪነ-ጥበብ ስራዎች ለውበት ብቻ የሚቀርቡ ሳይሆኑ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የጀርባ አጥንት ጭምርም ናቸው።
ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማትን ከማዋቀር ባሻገር የህዝብን ስነ-ልቦና እና የጋራ ማንነት መገንባትን ይጨምራል።
በዚህ ሂደት ኪነ ጥበብ እኔ ከሚል ግላዊ ስሜት ይልቅ እኛ በሚል የጋራ አስተሳሰብ በማስተሳሰር ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በመጨመር ታማኝነትን ያጸናል፡፡
በተለይ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ እና እምነት ባላቸው ሀገራት ውስጥ ኪነ ጥበብ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። የሰዎችን ህመም፣ ተስፋ እና ፍላጎት በጋራ ቋንቋ በመግለጽ አንዱ የሌላውን ስሜት እንዲረዳና እንዲጋራ ያደርጋል።
ልዩነቶችን አጥብቦ የጋራ እሴቶችን በማጉላት ረገድም የጥበብ ስራዎች ሚና የላቀ ነው። ስህተቶች ሲታረሙ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ሲመለሱ እንዲሁም ሙስና እና የአስተዳደር ጉድለቶች በጠራ መንገድ ሲተቹ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ማህበረሰባዊ እሴቶች ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀሩ እና አዳዲስ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች እንዲሰርጹ ለማድረግ ጥበብ ቀዳሚዋ ናት። ፖለቲካ የሀገርን መዋቅር ሲሰራ፣ ኪነ ጥበብ ደግሞ ማንነት እና መገለጫን ይቀርጻል።
የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ግጥሞች ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላ የሀገር ፍቅርን፣ ጀግንነትን እና መስዋዕትነትን የሚገልጹ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ናቸው። እነዚህ ግጥሞች ጀግኖችን ለማበረታታት፣ ለጠላት ጠንካራ አንድነትን ለማሳየት እና ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያገለግሉ ቀጥተኛና የሞራል ግንባታ መልዕክቶችን ይይዛሉ።
በቀደመው ዘመን የተዘጋጁ አያሌ የስነ ጽሁፍ ስራዎች፡ ቴአትሮች የክብር ዘበኛ እና የፖሊስ የጦር ሰራዊት ኦርኬስትራዎች እንዲሁም ስመ ጥር የሙዚቃ ባንዶች የሰሯቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች የሀገር ፍቅር ስሜትን በማጎልበት ረገድ የነበራቸው አስተዋጽዎ ከፍተኛ ነው፡፡
ባለንበት ዘመንም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሉዓላዊነት እያወደሱ የሀገሪቱን ብዝሃ ባህላዊ መሰረቶች የሚዘክሩ አያሌ የሙዚቃ እና የመድረክ ስራዎች አሉ።
ከግጥም፣ ከሙዚቃ እና ከሥነ-ጽሑፍ ወጎች ባሻገር፣ እንደ ሀውልቶች እና ምስሎች ያሉ ተጨባጭ የስነ-ጥበብ ቅርጾችም ህዝብን በማስተማር እና በማነሳሳት ረገድ እኩል የሆነ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
ለአብነት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ የቆሙት የኢትዮጵያ ጀግኖች ምስሎች ለአሁኑ ትውልድ የማይጠፋ የእይታ ትምህርት ይሰጣሉ። እነዚህ ሀውልቶች ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አርበኞችና የጦር መሪዎች በአንድነት ተነስተው የውጭ ወራሪን እንዴት በድል አድራጊነት እንደመከቱ ያሳያሉ።
ኢትዮጵያን እንደ ሉዓላዊ የነጻነት ምድር ብቻ ሳይሆን፣ የመላው የአፍሪካ አህጉርን የነጻነት ተስፋ ያቀጣጠለች እና የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄን የቀረጸች የነጻነት ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌት አድርገው በማሳየት፣ እነዚህ የስነ-ጥበብ ድንቅ ስራዎች አዲሱ ትውልድ አንድነቱን እንዲጠብቅ፣ ቅርሱን እንዲንከባከብ እና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና በንቃት እንዲወጣ ያነሳሱታል።
ኪነ ጥበብ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝቡን በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች አጽናንቶ ያቆየ በዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዞ መንገድ የቀየሰና እየቀየሰ ያለ ሀብት ነው።
በምሕረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.