Fana: At a Speed of Life!

በሕዝብ የባለቤትነት መንፈስ ዋዜማው ላይ የደረሰው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚካሄድበት ዋዜማ ላይ እንገኛለን። እዚህ ለመድረስ ባለፉት አራት ዓመታት ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ብዙ ተሰርቷል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በስምንት የተለዩ አጀንዳዎች ላይ ከነገ ጀምሮ ለመምከር ዝግጅት ተጠናቅቋል። በምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች አዲስ አበባ ከትመዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች መልክ ኢትዮጵያን የሚመስልና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተወከለበት እንዲሆን በጥንቃቄ ተሰርቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ጉባዔ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን ዝግጁ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እንደሚሉት÷ በሀገራዊ ምክክር ሒደት ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ምሕዳር ተፈጥሯል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል፤ በዚህም በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሥራ ተከናውኗል።

ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል በጉባኤው ወቅት ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ማብራሪያ የሚሰጡ ልሂቃን ማዘጋጀት አንዱ ነው።

ልሒቃኑ በምክክሩ ሒደት የጋራ መረዳት እንዲፈጠር፣ ውስብስብ ጉዳዮችን ታሪካዊ አመጣጥና የታዩ ክስተቶችን በጥናት አስደግፎ በማመላከት ወደ መፍትሄ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

ወደ ምክክር ጉባኤ የሚያደርሱ መሰረታዊ ተግባራት ሲያከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ እንዲሆን በተደረገው ጥረት በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 1 ሺህ 234ቱን ማሳተፍ ተችሏል።

ይህም 93 በመቶ የሚሸፍን መሆኑ የተደራሽነት አድማሱን የላቀ አድርጎታል።

የፌደራል ባለድርሻ አካላት፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በ12 ክልሎች ሰፊ እና ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ተከናውኗል።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም እንዲሳተፉ መደረጉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚመልስ ያደርገዋል።

አጀንዳ የተሰባሰበባቸው አካባቢዎች ለዋናው ጉባኤ የሚወክላቸውን ሰዎች መርጦ ልኳል።

የምክክር ሂደቱ ከጅምሩ አንስቶ ግልጽ፣ ገለልተኛ እና አሳታፊ በሆነ አሰራር እንዲመራ መደረጉ ከምክክር ሂደቱ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት መንገድ የጠረገ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሂደቱ የሰጠው ትኩረት እና ያሳየው የባለቤትነት መንፈስ እጅግ የሚያበረታታ ሲሆን፤ ሕዝቡ ታሪክ የማይረሳው ሀገራዊ ኃላፊነት ተወጥቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.