የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ ጨፌ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባዔው ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አንዲሁም የ2018 ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተሰሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ቀርበው ምክክር የሚካሄድባቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ በመደበኛ ጉባዔው የተለያዩ ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
በጉባዔው የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አቢዲሳ፣ የጨፌ አባላት፣ አባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች ተሳትፈዋል።
በአቤል ነዋይ