በክልሉ በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል – አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የሰላም፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶች እንዲሳኩ በተከናወኑ የቅንጅት ሥራዎች አኩሪ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን።
የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት 6ኛ የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን በዚህ ወቅት ÷ የዘንድሮው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባዔ ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ካጠናቀቀች በኋላ መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በመሠረተ ልማት፣ በሰላምና ደህንነት ሕብረተሰቡን ያሳተፉ በርካታ ሰው ተኮር ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ጨፌው የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በቅንጅት ማከናወኑን እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት፡፡
ጉባዔው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንዲሁም በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በመምከር አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም የ2019 ዓ.ም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቅድ ማስፈጸሚያ በጀትን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክሮ ያጸድቃል ነው ያሉት።
የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርቶች መርምሮ እንደሚያጸድቅም አፈ ጉባዔዋ ጠቁመዋል፡፡
በአቤል ነዋይ