የቱሪዝም መስህብ ባለፀጋዋ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት መካከል በባህል፣ በታሪክ፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ሀብት ግንባር ቀደም ከሆኑት ተርታ ትመደባለች።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የመዘገባቸው በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶችም ባለቤት ናት።
ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እስከ አክሱም ሐውልቶች፤ ከጢያ ትክል ድንጋይ እስከ ጎንደር ፋሲለደስ፤ ከሐረር ጀጎል እስከ ኦሞ ስምጥ ሸለቆ፤ ከባሌ ብሔራዊ ፓርኮች እስከ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ ወ.ዘ.ተ ያሉ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ባለ ብዙ የቱሪስት መዳረሻ ናት ኢትዮጵያ።
እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ገዳ ስርዓት፣ ፍቼ ጫምባላላና ጊፋታ በዓል ያሉ ቀልብን የሚገዙ ባህላዊ መስህቦችንም በቅጥሯ ጉያ ሸሽጋ የዓለምን ትኩረት የሳበች ሀገርም ነች፡፡
የእነ ድንቅነሽ (ሉሲ)፣ አርዲ (ሰላም) እና የሌሎች የሰው ልጅ ጥንታዊ ቅሪተ-አካላት የተገኙባት፤ ለሳይንሳዊ ምርምር እና ቱሪዝም ሰፊ አቅምን የተቸረች ምድረ ቀደምት።
ርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት፤ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ዩኤንኢሲኤ) ብሎም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ በየዓመቱ ብዙዎች ወደዚህች ከተማ ይተምማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን የመሰሉ ለጉባኤዎች አመቺ ስፍራዎችን በመያዝ ለስብሰባዎችና ለዲፕሎማቲክ ቱሪዝም ያላት ሳቢነት አያጠያይቅም።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይዞት ብቅ ያለው የንጋት ሀይቅና በእርሱ ላይ የሚገኙት ከ70 በላይ ደሴቶች ለቱሪዝሙ ዘርፍ ተጨማሪ ስንቅ ናቸው፡፡
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተገነቡት የገበታ ለሸገር ፍሬዎች ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲሆኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እውን የሆኑት መዳረሻዎች እንዲሁም የኮንፍረንስ ማዕከላት የሀገሪቱን የቱሪዝም አቅም በእጥፍ ያሳደጉ ጸጋዎች ሆነዋል።
አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር በማገናኘት ሰፊ የበረራ መረብ ያለው የአህጉሪቱ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ በረራዎቹ የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ይህ ሰፊ ሀብትና የመደመር መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትልቅ ትኩረት፤ ኢትዮጵያን የመስህብ ባለፀጋ፤ ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን የኢኮኖሚ ጥቅምም እንዲሰፋ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በመልካም ፈቃዱ