የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት እንዲከበር ዝግጀት ተደርጓል – ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት እንዲከበር በቂ ዝግጀት ተደርጓል አሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር የመስቀል ደመራ በዓል የቅደመ ዝግጀት ስራዎችን አስመልክቶ ምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በመድረኩ÷ የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበርና ብዙ ህዝብ የሚታደምበት የአደባባይ በዓል መሆኑን አንስተዋል።
በዓሉን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ እና በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበ መሆኑን አስታውሰው፤ የመስቀል ደመራ በዓልን የሀገርን ገፅታ በሚገነባና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሀይማኖት አባቶች በበዓሉ የተከለከሉ ነገሮችን ለምዕመኑ በማሳወቅ እንዲሁም ከፀጥታ አካሉ ጋር በቅንጅት በመስራት በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር በበኩላቸው÷ በዓሉ ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ከህዝቡ እና ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በቤተክርስቲያኗ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ብርሀን ሰለሞን በቀለ÷ በዓሉን ስናከብር የመስቀሉን ታላቅነት በማስቀደም፣ አንድነትን መሰረት በማድረግ እና ሀይማኖታዊ ትውፊቱን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በሳራ ስዩም